ለ67ሺ 856 ለሚሆኑ የከተማችን ስራ ፈላጊዎች ቋሚ የሥራ ዕድል ተፈጠረ
የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ የሥራ ስምሪትና ምግብ ዋስትና ዘርፍ በሁለት ወራት 67ሺ 856 ለሚሆኑ የከተማችን ስራ ፈላጊዎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠሩን ገለፀ።
ጳጉሜን 03/2017 ዓ ም የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ የሥራ ስምሪትና ምግብ ዋስትና ዘርፍ የቢሮውና የክ/ከተማ ፈፃሚዎችና አመራሮች በተገኙበት የሀምሌና የነሀሴ ወር አፈፃፀሙን ገምግሟል። በግምገማ መድረኩ ባለፉት ሁለት ወራት 67ሺ 856 ለሚሆኑ የከተማችን ስራ ፈላጊ ነዋሪዎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር የተቻለ ሲሆን ከተፈጠረው የሥራ ዕድል ውስጥ 13ሺ 949 የሚሆኑትን በ2ሺ 645 ኢንተርፕራይዞች በማደራጀት የተፈጠረ መሆኑ ተገልጿል። የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ሠሪ ሀይሎችን በት/ቤቶችና በጤና ጣቢያዎች በከተማ ግብርና በማሰማራት ወደ ስራ እንዲገቡ ከማድረግ አንፃር የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በመድረኩ ተገልጿል። የግምገማ መድረኩን የመሩት የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ የሥራ ስምሪትና ምግብ ዋስትና ዘርፍ ኃላፊ አቶ አስፋው ለገሠ ከሥራ ዕድል ፈጠራ አንፃር ከቅጥር ባሻገር ኢንተርፕራይዞችን ማደራጀት ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል። አቶ አስፋው በመድረኩ በሰጡት ማጠቃለያ በየአካባቢው ያሉ ፀጋዎችን በተቀመጠው መስፈርት መሠረት በመለየት የምንሰጣቸው ስልጠናዎችና የምንፈጥራቸው የሥራ ዕድሎች የለየናቸውን ፀጋዎች መሠረት ያደረገ መሆን እንዳለበት አቅጣጫ አስቀምጠዋል። በግምገማ መድረኩ የማዕከል የዘርፉ ሠራተኞች እና የክ/ከተማ ምክትል ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ የቡድን አስተባባሪዎችና መሪዎች ተገኝተዋል።
No comments yet. Be the first to comment!